በሐረር ከተማ ለልማት ተነሺ ዜጎች የቤት መገንቢያ መሬት ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ባለስልጣን አሰታወቀ።
በሐረር ከተማ ከደሴ ሆቴል እስከ አቦከር ሙጢ በሚከናወነው የመንገድ ልማት ከአካባቢው ተነሺ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ባለ ስልጣን ሀላፊ አቶ ጁነዲን ኑረዲን ገለፁ።
በዚህም መሰረት ከአካባቢው የተነሱ ዜጎችን መልሶ ለማስፈር ከ 3 ሄክታር በላይ የቤት መገንቢያ የመሬት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከልማት ተነሺዎቹ ውስጥ ከ 85 በላይ የሚሆኑት የመንግስት ሲሆን ከ35 በላይ የግል ይዞታዎች መሆናቸውንም አክለዋል።
የልማት ተነሺዎችን የቀድሞ ማህበራዊ ህይወትና ትስስር ሳይቋረጥ ለማስቀጠል ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረዉ አካባቢ ብዙም ሳይርቁ በ 600 ሜትር ርቀት ላይ ለማስፈር እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ይህም የልማት ተነሺዎችን ማህበራዊ ህይወት ከማስቀጠል ባሻገር የአካባቢውን ኢኮኖሚ ይበልጥ ለማነቃቃት የሚያስችል ነው።
የልማት ተነሺዎቹ በመኖሪያ ቤት ግንባታ የዲዛይን እና የግንባታ ዶክመንቶች እንዲሟሉላቸው አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ ጁነዲን ኑረዲን ገልፀዋል።
በክልሉ የልማት ሂደት የሚነሱ ዜጎችን ሳይጉላሉ መልሶ ለማስፈር አስፈላጊው የመሬት ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።






