የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከሐረሪ ብ/ክ/መ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር በመሆን በሐረር ከተማ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በመተግበር ላይ ይገኛል።
የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላቸው ፀሐይ የተመራ የሉካን ቡድን በሐረር ከተማ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ሙከራ እና የመስክ ላይ ቅኝት ስራዎች ተደርጓል።
በዚሁ መርሃግብር የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ በላቸው ፀሐይ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ በበጀት ዓመቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ከሚደረጉ ከተሞች እንዱ መሆኑን አውስተው፣ በሐረር ከተማ የተተገበረው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት እና የአድራሻ ጠቋሚ ምልክቶች እና ዲጂታል የቤት ቁጥሮች በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ይህ የአድራሻ ሥርዓት የሐረር ከተማን ይበልጥ ለጎብኝዎች የምትመች እና ለከተማዋ ሰፊ የኢንቨስትመት ምንጭ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የሐረሪ ክልል የከተማ ልማት እና ኮንስትራክን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በሐረር ከተማ ላይ እያከናወነው ያለውን የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ትግበራ አስመልክቶ ለኢንስቲትዩቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አቶ ሙክታር አክለው እንደገለጹት የሐረር ከተማ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ክልሉ በስትራቴጂክ እቅድ ከያዛቸው እና በክልሉ ፕሬዘዳንት ጭምር ክትትል ከሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች እንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ፕሮጀክትም እንደ ክልላችን አቅደን የመፈጸም አቅማችን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ማናጀር አቶ አግማሴ ገበየሁ እንደገለጹት፣ የፕሮጀክቱ በተያዘው እቅድ ለመጠናቀቁ በሁለቱም በኩል የነበረው አመራርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ቁርጠኝነት መሆኑን በማውሳት፣ የሐረር የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ትግበራ ለሌሎች ከተሞችም እንደ ተምሳሌት የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።
አያይዘውም የሐረር ከተማ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መጨረሻ ተመርቆ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።





