ፕላን ኢንስቲትዩት
መግቢያ
አለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ አገራዊና ክልላዊ የከተሞች ሚና በመንግስታቱ ተለይቷል። የሁሉም ራዕይ “ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል ማድረግ” ነዉ። ራዕይዉ እዉን መሆን የሚችለዉ ከተሞች በከተማ ፕላን መመራት ሲችሉ ብቻ ነዉ። ከ2000 ህዝብ በላይ ተጠጋግቶ ከሚኖርበት የገጠር የልማት ማዕከላት ጀምሮ እስከ ሜትሮፖሊታን ያሉ ከተሞች በሙሉ የየራሳቸዉ የሆነ የከተማ ፕላን ያስፈልጋቸዋል። እያንዳንዱ ከተማ የራሱ የሆነ ወሰን ቢኖረዉም በዙሪያዉ ካለዉ የገጠር ልማት፣ ከአከባቢዉ ሌሎች ከተሞች ጋር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከባቢያዊ ልማት የሚተሳሰርበትና የሚለማበት የትሥሥር ፕላን ያስፈልገዋል። አገራዊና ክልላዊ የከተማ ዘርፍ የ10ዓመት መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቷል። በዚህ መሪ ዕቅድ፣ በመንግስት የወጡና የፀደቁ የከተማ ዘርፍ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም አለም አቀፋዊ፣ አገራዊና ክልላዊ የከተማ ዘርፍ ጥናት ሰነዶች ላይ እንደተመለከተዉ የሀረሪ ክልል ክትመት 100% የሚደርስ መሆኑንና ይህንን ክትመት በከተማ ፕላን መምራት የህልዉና ጉዳይ መሆኑን ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ራዕይ (Vision)
የኢንስቲትዩቱ ራዕይ “ ከተሞቻችን የብልጽግና ማዕከል ሆነዉ ማየት” ነዉ።
የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት ራዕይ ከላይ የተመለከተዉ አገራዊና ክልላዊ የከተማ ሴክተር ራዕይ ነዉ። በዚህ ራዕይ ላይ “ከተሞቻችን” የሚለዉ ቃል የሀረር ከተማንና በቀጣይ ወደ አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች የሚያድጉ የገጠር ቀበሌዎችን ማለት ነዉ። “ብልጽግና” የሚለዉ ቃል የፓርቲ ስም ሳይሆን በአለም አቀፍ፣ በአህጉር፣ በአገርና በክልል ደረጃ የጋራ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ሎጎ ሲሆን የበለጸገ ከተማ የሚባለዉ ቀጣይነት ያለዉ የከተማ ምርታማነት ያደገበት፥ ስልጡ መሰረተ ልማትና አገልግሎት የቀረበበት፥ የተሻለ የኑሮ ደረጃ የሰፈነበት፥ አካታችና እኩልነት የተረጋገጠበት እና ለአየር ንብረትለዉጥ የማይበገር ዘላቂ አከባቢ የተፈጠረበት ከተማ ማለት ነዉ።
የኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ
የኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ:
“ ክትመታችን የገጠር ዕድገትን የሚያፋጥን፣ መሬትንና ሌሎች ሀብቶችን በቁጠባ የሚጠቀም፣ የሰዉ እና የምርቶችን እንቅስቃሴ የሚያፈጥን፣ ለአከባቢ ተፅዕኖ የማይበገር፣ አካታች፣ አሳታፊና ዘላቂ ልማትን የሚያቀናጅ ተዋረዱን የጠበቀ የከተማ ፕላን በማዘጋጀትና በማስተግበር የከተሞቻችንን የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጥ ነዉ “።
ከላይ የተመለከተዉ የከተማ ብልጽግና የሚሰፍነዉ በከተማ ፕላን መመራት ሲችሉ ብቻ ነዉ። የከተማ ፕላን ለከተሞች ልማት እና ለሁሉም የከተማ ነዋሪ ተመጣጣኝና ፍትሃዊ የከተማ መሬት የሚደለድል፣ የድሃና የሀብታም፥ የህዝብና የመንግስት፥ የልማትና የአከባቢ ጥበቃን በአጠቃላይ ተቃራኒ ፍላጎቶችን በማስታረቅ የተደላደለ አከታተም የሚያሰፍን የከተሞች ብልጽግና መንገድ(መሳሪያ) ነዉ። በመሆኑም የኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ ከከተማ ፕላን ባህርይና ከከተሞች የብልጽግና ምሰሶዎች የተቀዳ ነዉ። በተልዕኮዉ ዉስጥ የመጨረሻ ሀረግ “ የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጥ” የሚለዉ ሀረግ የከተማ ፕላኑና ልማቱ የከተሞች ብልጽግና መለኪያ ኤንዴክስ (CPI) መሰረት ወደ ተፈለገዉ የብልጽግና ጉዞ እየሄዱ መሆኑን በመገምገም አፋጣኝ መፍትሄን በከተማ ፕላን ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ያሳያል።
የኢንስቲትዩቱ ሥልጣንና ኃላፊነት
የኢንስቲትዩቱ ተጠሪነት ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሆኖ የሚከተሉ ሥልጣንና ኃላፊነት አሉት።
-
የከተማ ፕላን ለማዘጋጀትና የተለያዩ ፕላን አስፈጻሚ ተቋማትን ስፓሻል መረጃ ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሰረታዊ ካርታዎችን በተለያዩ መስፈርቶች ያዘጋጃል፣ ያሻሽላል፣ ያጸድቃል፣ ሥራ ላይ እንዲዉሉ ያደርጋል።
-
ለመሰረታዊ ካርታ ዝግጅት የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን ይለያል፣ ዝርዝር ስፔሲፊኬሽን ያዘጋጃል፣ በግዢና በተለያዩ ድጋፎች እንዲሟሉ ያደርጋል፣ በአግባቡ ሥራ ላይ ያዉላል።
-
ለመሰረታዊ ካርታ ዝግጅት፣ ለከተማ ፕላን ዝግጅት፣ ለመሬት አጠቃቀም፣ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታና ቅንጅት የሚያስፈልጉ የሳተላይት ምስል እና ወይም፣ የአየር ላይ ፎቶግራፍ እንዲሟሉ ያደረጋል፣ የመሬት ላይ ቅየሳ መቆጣጠሪያ ነጥቦች እንዲሟሉ ያደርጋል።መረጃዎቹን ከፌዴራል ጂኦዴቲክ የቅየሳ መቆጣጠሪያ መረብ ጋር ያቀናጃል፣ እርስበርሳቸዉ መናበባቸዉን ያረጋግጣል፣ ለዚህ ሥራ የሚያስፈልጉ ሃርድዌሮችንና ሶፍትዌሮችን ያሟላል፣ የአጠቃቀም ስታንደርድ ያዘጋጃል፣ ያጸድቃል ተግባራዊነታቸዉን ይቆጣጠራል።
-
ለከተማ ፕላን ተዋረድ መነሻ የሆኑትን አገራዊ የከተማ ልማት ስኪምን ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በማጣጣም ግንዛቤ እንዲያዝ ያደርጋል፥
-
የክልሉን አጠቃላይ የከተማ ልማት አቅጣጫ የሚያሳይ ክልላዊ የከተማ ልማት ስፓሻል ፕላን ያዘጋጃል፣ ወይም እንዲዘጋጅ ያደርጋል፥ የማስተግበሪያ ክልላዊ ስትራቴጂ ያዘጋጃል፣ ያጸድቃል ፣ ለሌሎች የከተማ ፕላን ግብዓትና መነሻ እንዲዉሉ ያደርጋል።
-
የከተማ መዋቅራዊ ፕላን፣ የስትራቴጂያዊ ፕላን፣ የመሰረታዊ ፕላን፣ የሰፈር ልማት ፕላን፣ የከተማ ዲዛይን ፕላን፥ የከተማ ብሎክ ዲዛይን ፕላን፥ የሚዘጋጅበትን እና የትግበራ ክትትልና ግምገማ ስታንደርዶችን፣ ኖርሞችንና ማኑዋሎችን ያዘጋጃል፣ ወይም በፌዴራል የተዘጋጁትን ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ያጣጥማል፣ ያጸድቃል፣ ሥራ ላይ ያዉላል።
-
የከተማ መዋቅራዊ ፕላን፣ የስትራቴጂያዊ ፕላን፣ የመሰረታዊ ፕላን፣ የሰፈር ልማት ፕላን፣ የከተማ ዲዛይን ፕላን፥ የከተማ ብሎክ ዲዛይን ፕላን ያዘጋጃል፣ ወይም እንዲዘጋጁ ያደርጋል፣ ነባሮቹን ያሻሽላል፣ ያጸድቃል፣ ተግባራዊ እንዲሆኑ አቅም ይገነባል፣ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ ይቆጣጠራል፣ ያረጋግጣል።
-
የከተማ ፕላን ጥሰቶችን ያጠናል፣ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ያዛል፣ መስተካከሉን ይከታተላል፣ በህግ አግባብ እርምጃ ይወስዳል ወይም ያስወስዳል፣
-
የከተማ መለጠጥ፣ የከተማ ማርጀትና መተፋፈግ፣ የከተማ መስፋፋት ጥናቶችን ያጠናል፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል፣ ሲፈቀድ የከተማ ማደስ፣ ማሻሻልና ማስፋፋት ፕሮግራም ይቀርጻል፣ ያጸድቃል፣ ተግባር ላይ ያዉላል\እንዲዉሉ ያደርጋል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ የፋይዳ ጥናት ያከናዉናል።
-
የገጠር ቀበሌዎችና ወረዳዎች የከተማ ዕዉቅና የሚያገኙበትን ጥናት ያጠናል፣ የከተማ ደረጃና አደረጃጀት እና የህጋዊ ሰዉነት ማቋቋሚያ ህግ ማዕቀፋትን ያዘጋጃል፣ ያስተቻል፣ ያጸድቃል፣ ተግባራዊ እንዲሆኑ አቅም ይገነባል፥ ተግባር ላይ መዋላቸዉን ይከታተላል፣ ይደግፋል።
-
የገጠር ቀበሌዎችና ወረዳዎችን የከተማ ፕላን ከወረዳዎቹና ከህዝቡ ጋር በመመካከር ተገቢ የከተማ ፕላን ያዘጋጃል፣ የማስተግበሪያ ፕሮጀክቶችን ይነድፋል፣ ያጸድቃል፥ ተግባራዊ እንዲሆኑ አቅም ይገነባል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ ድጋፍ ይሰጣል\እንዲያገኙ ያደርጋል።
-
በቅርስና አርኪዮሎጂካል ሳይት፣ ከመከላከያና ደህንነት ተቋማት ሳይት ዉጪ ባሉ በሀረር ከተማ ለሚካሄዱ ማንኛዉም የህንጻ ግንባታዎች፥ የመንገድና ተያያዥ መሰረተ ልማቶችና ፋሲሊቲዎች፥ ለአረንጓዴ መሰረተ ልማትና ተያያዥ ልማቶችና አከባቢ ጥበቃ ሥራዎች ከከተማ አቀፍ እስከ ይዞታ ደረጃ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የፕላን መረጃና የፕላን ስምምነት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ይሰጣል፥ የከተማ ፕላኑን ጠብቀዉ ስለመገንባታቸዉ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣ ግንባታዎቹ ሲጠናቀቁ በቤዝ ማፕ ያወራርሳል። የግንባታዎቹንና የልማቱን ፋይዳ ያጠናል።
-
የገጠርና የወረዳ ከተሞች የፕላን ስምምነት አሰጣጥ በሚዘጋጅላቸዉ ፕላንና በማቋቋሚያ ህጎቻቸዉ የሚወሰን ሲሆን ለአስፈጻሚዎቹና ለሙያተኞቹ የቴክኒክና የክህሎት አቅም ይገነባል፥ የቴክኒክ መሳሪያዎችና ዘመናዊ ሶፍትዌሮችን በማጥናት እንዲሟሉላቸዉ ያደርጋል። ለአጠቃቀማቸዉ ሥልጠና ይሰጣል።
-
የክልሉን ከተሞች ፕሮፋይል ያዘጋጃል።
-
የከተሞች የዘላቂ ልማት ግቦች (SDG11)፣ የከተሞች ብልጽግና ግቦች (CPI)፣ የከተሞች የአየር ንብረት ለዉጥ በካይ ጋዞች ልቀት መቀነሻ (Mitigation) እና የተፅዕኖ መቋቋሚያ (Adaptation) ቴክኖሎጂዎች ስላስገኙት ጥቅም ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን የከተማ ዘርፉን ጥናት ያከናዉናል፣ የጥናት ዉጤቱን ያሳዉቃል።
-
በከተማ ፕላን ዝግጅትና ትግበራ የባለድርሻ አካላትና የህዝብ ተሳትፎን ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ያረጋግጣል።
-
የከተማ ፕላን ዝግጅት አማካሪ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ይመዘግባል፥ ለክልሎች በተሰጠ ስልጣን መሰረት ፈቃድ ይሰጣል፣ ያድሳል፣ ይሰርዛል።
-
ከሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር የሚኖሩ የከተማ ፕላን ጉዳዮችን ክልሉን ይወክላል።
-
የከተማ ፕላን ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን፣ አጋሮችን፣ ህዝቡንና ባለሙያዎችን አቅም ይገነባል።
-
የኢንስቲትዩቱን የሰዉ ኃይል ያስወስናል፣ ይመራል፣ ያስተዳድራል።
-
የኢንስቲትዮቱን ፕሮግራም፣ ፕሮጀክት፣ ዕቅድና በጀት ያዘጋጃል፣ ያጸድቃል፣ ተግባራዊ ያደርጋል።
-
ከሥራዉ ጋር በተያያዘ ለሚሰጠዉ አገልግሎት ክፍያ ያስከፍላል።
-
ተቋሙን በመወከል ዉል ይዋዋላል፣ በስሙ ንብረት ያስተዳድራል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል።
-
ከቢሮዉ የሚሰጡ ሌሎች ሥልጣንና ኃላፊነት ይኖሩታል።
