Thursday, April 30, 2026
HomeMeetingCommunityየክልሉ መንግስት ያዘጋጀውን ምትክ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተረክበናል፦ የልማት ተነሺዎች

የክልሉ መንግስት ያዘጋጀውን ምትክ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተረክበናል፦ የልማት ተነሺዎች

በሀረሪ ክልል አቦከር ወረዳ ከደሴ ሆቴል እስከ አቦከር ሙጢ ለሚከናወነው የመንገድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስራ የልማት ተነሺዎች የክልሉ መንግስት ቃል በገባላቸው መሰረት ምትክ የቤት መስሪያ ቦታ መረከባቸውን ገለፁ።

የልማት ተነሺዎቹ እንደሚሉት በክልሉ ከደሴ ሆቴል እስከ አቦከር ሙጢ የሚከናወነው የመንገድ ፕሮጀክት ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር የቀበሌና የግል ይዞታቸውን በፈቃደኝነት በመልቀቅና በማፍረስ ለልማቱ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ገልፀዋል።

የመንገድ ልማት ስራው ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍና ለነዋሪዎች ምቹ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም የልማት ተነሺዎቹ ጨምረው ገልፀዋል።

በዛሬው እለትም የክልሉ መንግስት ያዘጋጀላቸውን ምትክ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መረከባቸውን የልማት ተነሺዎቹ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በተሰጣቸው ምትክ የቤት መስሪያ ቦታ መደሰታቸውን ገልፀው ለክልሉ መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም ምትክ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንደማይሰጠን ሲሰራጩ በነበሩ የተሳሳቱ መረጃዎች ሃሳብ ገብቶን ነበር ያሉት የልማት ተነሺዎቹ አሁን ግን የክልሉ መንግስት የዜጎችን መብትና ጥቅም ማዕከል ያደረገ ልማት እያከናወነ ስለመሆኑ ለመረዳት ችለናል ብለዋል።

የሀረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ረኢስ ዩሱፍ በክልሉ ከደሴ ሆቴል እስከ አቦከር ሙጢ ለሚከናወነው የመንገድ ልማት 50 የቀበሌና 24 የግል ይዞታ ለነበራቸው የልማት ተነሺዎች ምትክ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን ገልፀዋል።

በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ለቀሩት 29 የቀበሌ እና 9 የግል ይዞታ የልማት ተነሺዎች የቤት መስሪያ ቦታው እንደሚሰጣቸውም ጠቁመዋል።

የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታው የልማት ተነሺዎችን ማህበራዊ መስተጋብርን ባስጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱን አቶ ረኢስ ተናግረዋል።

በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ጁኔድ ኑረዲን በበኩላቸው ምትክ መሬት ለተሰጣቸው የልማት ተነሺዎች በቀጣይ ሳምንት የግንባታ ፍቃድ እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል።

በክልሉ በ2018 በጀት አመት ለመኖሪያ ቤት መስሪያ 6 ሄክታር የሚሆን የመሬት ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

RELATED ARTICLES

Most Popular

Recent Comments