በመሬት አስተዳደር ስርዓት ውስጥ የመሬት መረጃን በዘመናዊ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ስርዓት ማስተዳደር እጅጉን አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ መሬትን ማስተዳደር እና መምራት ብሎም ከዘርፉ የሚገኘውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማይቻል ነው፡፡ ስለሆነም የመሬት መረጃን በአግባቡና በዘመናዊ መልኩ ማደረጃት ጥያቄ ውሥጥ የሚገባ አይደለም በማለት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙኽታር ሳሊህ ገልጸዋል ።
የማህደር አደረጃጀትና አጠባበቅ ካሁን በፊት ብዙም ትኩረት የተሰጠው ባለመሆኑ እንዲሁም ተከታታይነት ባለው መልኩ ሲሰራ ስላልነበር የይዞታ መረጃዎች በዘፈቀደ በተበታተነ እና ባልተደራጀ መልኩ የተቀመጡበት አግባብ በሰፊው ይሰተዋላል፡፡ በዚህም የመሬት ይዞታ መረጃዎች ተደራጅቶ ባለመቀመጡና በሚገባ መልኩ ጥበቃ ያልተደረገላቸው በመሆኑ የከተማ ቦታን ለህገ-ወጥ ወረራና ለኪራይ ሰብሳቢዎች በር በመክፈት ውስን የሆነውን የከተማ መሬት ለታለመለት አላማ ለማዋል አዳጋች በመሆኑ የይዞታ ማህደሮች በአግባቡ ባለመደራጀቱ ምክንያት ዘመናዊ የማህደር አያያዝ ስርዓት መዘርጋት አልተቻለም ፡፡
በከተማችን የሚገኙ የመሬት ይዞታ በማህደር በአግባቡ ማደራጀት ከሚሰጡት ጥቅሞች መካከል አንደኛ በዘርፉ የሚገኛውን ገቢ ከፍ በማድረግ የከተማችንን እድገት የሚያፋጥን ሲሆን ሁለተኛው እና ዋነኛው ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራትን ለመስበር አይነተኛ ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም የባለይዞታውን የባለቤትነት ዋስትና ለመስጠት እና የተቀላጠፈ የይዞታ ማህደር አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ሚናው የጎላ ያደርገዋል፡፡
በመሆኑም የተቋማችን ማህደሮች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉና በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥናት በማድረግ የተደራጁ ማህደሮችን በማንና በምን መልኩ እንደተከናወኑ ማወቅ፤በአግባቡ የተደራጁና ያልተደራጁ ማህደሮችን የመለየት ፤ በተደራጁ ማህደሮች ውስጥ ያሉ መረጃዎችን በሚዘጋጀው ሶፍትዌሮች ላይ መጫን እንዲሁም ኢንኮድ በማድረግ በተጨማሪ ያልተደራጁትን ማደራጀት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙኽታር ሳሊህ ስራው ያለበትን ደረጃ በመጎብኘት ገምግሞ በቀጣይ ቀሪ ስራዎችን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በርብርብ እንዲሰራና በመሬት አስተዳደር ላይ የሚታዪ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ብሎም የህብረተሰቡን ጥያቄ በሚገባ በመመለስ የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት እንደሚገባ ገልፀዋል።









