ሀረር መስከረም 12/2017(ሀክመኮ):- በሀረሪ ክልል ተግባራዊ በሚደረገው የሰፈር ፕላን ህብረተሰቡ መረጃዎችን በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክተል ሀላፊ አቶ ረኢስ ዩሱፍ ጥሪ አቀረቡ። የሀረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በሀኪምና አቦከር ወረዳ ተግባራዊ በሚደረገው የሰፈር ልማት ኘላን ላይ የወረዳዎቹን ነዋሪዎችን አወያይቷል። የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት ዕና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ረኢስ ዩሱፍ ፕላኑ በክልሉ ሁለት ወረዳዎች አምስት አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልፀዋል። ኘላኑ የህብረተሰቡን ፍላጎት መነሻ በማድረግ ቤት ለቤት ከህብረተሰቡ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በማካተት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ገልፀዋል። ኘራይም ኮንሰልታንሲ ድርጅት ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ መረጃዎችን እንደሚሰበስብ የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ሀላፊው ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮች እና ፍላጐት ላይ ሃሳብቸውን መስጠት እንደሚገባቸው ገልፀዋል። የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈርሃን ዚያድ በበኩላቸው የሀረር ከተማን እድገት ለማሻሻል በከተማው ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በክልሉ ገቢራዊ እየሆኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማቶች የከተማውን ገፅታ ከማሻሻል በተጨማሪ የማህበረሰቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውንም አክለዋል። በመሆኑም የተጀመሩ የልማት ስራዎች በተያዘላቸው ግዜ በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማህበረሰቡ እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመድረኩ ፕላኑ ተግባራዊ የሚደረግባቸው የሀኪም እና አቦከር ወረዳ አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል



