ሀረር ጳጉሜ 3 /2016(ሀክመኮ):- በደም እና ላብ የተረጋገጠውን ሉዓላዊነት በልማት እና ብልፅግና ለመድገም ርብርብ እንደሚደረግ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በሀረሪ ክልል ጳጉሜ 3 – የሉዓላዊነት ቀን “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት”በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል። የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ኢትዮጵያ ለዘመናት ክብሯና ነፃነቷ ብሎም የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ የቆየች የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን ዕለቱን በማስመልከት በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ገልፀዋል። ይህም የሆነው በጠንካራ እና ፅኑ አቋም ላይ በሚገኘው ሰራዊቷ እና ደጀን የሆነው ህዝቧ መሆኑን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ በዘመናት ቅብብሎሽ የተቃጣባትን አደጋ በጀግኖች ልጇቿ መክታ ድል በማድረግ ታፍራ እና ተከብራ ሉዓላዊነቷን አስከብራ መኖሯን በመጠቆም ይህንን ድል አድራጊነት በልማት እና ብልፅግና ለመድገም ርብርብ እንደሚደረግ ገልፀዋል። አሁንም ቢሆን ከውስጥ እና ከውጭ ሆነው ኢትዮጵያን ለመውጋት የሚያሴሩ የጠላት ሀይሎች መኖራቸውን በመጠቆም ጥንት አባቶች ጠላትን አንገት ያስደፉበትን የአብሮነት፤የመደጋገፍ እና የጀግንነት ገናና እሴት በመላበስበ በአንድነት ለአገራችን ዘብ መቆም አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። ልማት እና ዲሞክራሲን ከሰላም ውጪ ማሰብ እንደማይቻል የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን ላይ በአገሪቱ ለሰፈነው ሰላም የህይወት መስወትነት የከፈሉ ጀግኖችን ማሰብ እና መዘከር ብሎም ክብር መስጠት እንደሚገባ አስገንዘበዋል። አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ውድ የአገር ልጆች መስዋት መክፈላቸውን በማስታወስ አገር የምትገነባው በዘመናት የትውልድ ቅብብሎሽ እና ጠንካራ እሴቶች በመሆኑ ይህ ትውልድ እነዚህን እሴቶች ጠብቆ የማቆየት ሀላፊነት እንዳለበት ገልፀዋል። በመሆኑም ከተረጂነት በመላቀቅ ጠንካራ ኢኮኖሚን በመገንባት እራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ትውልዱ የበኩሉን አሻራ ማኖር እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል። አክለውም ከጥንት አባቶቻችን የተረከብናትን ስመ ገናና ሉዓላዊ አገር ከአደጋ ለመከላከል ዝግጁነት ያለው ትውልድ መገንባት እንደሚገባ አስረድተዋል። በመጨረሻም መጪው አዲስ ዓመት የሰላም እና ብልፅግና እንዲሆን ርዕሰ መስተዳድሩ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል። የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ በበኩላቸው በክልሉ ያለውን አውንታዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም በሚል መርህ በክልሉ ቀድመው የነበሩ የአብሮነት እሴቶችን ይበልጥ እንዲጎለብቱ በማድረግ እና በመጠቀም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ገልፀዋል። ጳጉሜ 3 የሰንደቅ አላማ ስነ ስርዓትን ጨምሮ በፓናል ውይይት የተከበረ ሲሆን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፤የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ፤ የሀረሪ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድን ጨምሮ የክልሉ አመራሮች የፀጥታ ተቋማት እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
