Thursday, April 30, 2026
HomeMeetingCommunityየመሬት ማረጋገጥና ምዝገባ ስርአት {ካዳስተር} ማለት ምን ማለት ነው?

የመሬት ማረጋገጥና ምዝገባ ስርአት {ካዳስተር} ማለት ምን ማለት ነው?

ካዳስተር ማለት የመሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥርዓት ሲሆን የሚደራጁት መረጃዎችም በዋናነት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡

ይኸውም የካርታ መረጃ (spatial data) የይዞታውን መገኛ ቦታ፣ ወሰኑን፣ ስፋቱንና ቅርፁን፣ አጎራባች ይዞታዎችን እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ሲሆን ሌላኛው ገላጭ መረጃ (non-spatial data) በመባል የሚታወቀው የባለይዞታውን ማንነት (ስም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ወዘተ.)፣ በይዞታው ላይ ያለው መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት፣ የቦታው አገልግሎትና ደረጃ፣ ወዘተ… እንደ ካዳስተር ዓይነቱ ተዘርዝረው የሚያዙ መረጃዎችን ያካትታል፡፡

እነዚህ ሁለት የመረጃ ዓይነቶችም በልዩ የይዞታ መለያ ኮድ እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡

ካዳስተር በሦስት ዓይነት ይከፈላል፡-

👉አንደኛው ህጋዊ ካዳስተር ሲሆን ለእያንዳንዱ ህጋዊ ወሰን ለተለየለት ይዞታ፣ የይዞታ መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት የሚያመለክት መረጃ ከይዞታው ካርታ ጋር አጣምሮ የያዘ ወቅታዊ የመሬት ይዞታ መረጃ ሥርዓት ሲሆን አስፈላጊነቱም የትኛው ይዞታ በማንና በምን አግባብ ተይዟል የሚለውን በማጣራት የባለይዞታውን የይዞታ ዋስትና ለማረጋገጥ ነው፡፡

👉ሁለተኛው ዓይነት ፊስካል ካዳስተር ሲሆን በይዞታው ላይ ስላረፈው ቋሚ ንብረት ዝርዝር መረጃ እና የመሬቱን ወቅታዊ ግምት ከይዞታው ካርታ ጋር የሚይዝ ሆኖ ለቦታና ለንብረት ግብር ክፍያ የሚያገለግል ሥርዓት ነው፡፡

👉 ሦስተኛው ዓይነት ካዳስተር ሁለገብ/ሁሉን አቀፍ ካዳስተር/ የሚባለው በሁለቱ የካዳስተር ዓይነቶች የተገለፁትን መረጃዎች የሚይዝ ሆኖ በተጨማሪም የመሰረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች መረጃዎችን እና ካርታን አካቶ የሚይዝ የመረጃ ሥርዓት ነው፡፡

በመሆኑም በቅድሚያ ባለይዞታውን ተጠቃሚ የሚያደርገው ከተማ አስተዳደሮችም መሬታቸውን ቆጥረው ሊያውቁ የሚችሉበትን የህጋዊ ካዳስተር በመዘርጋት በመቀጠልም የፊስካል ካዳስተር ብሎም ወደ ሁለገብ ካዳስተር የሚያድግ ሥርዓት መዘርጋቱ ሥርዓቱን ቀጣይ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ተመርጧል፡፡

በዚህ ሂደት የካርታው መረጃ አንድ ጊዜ የሚዘጋጅ ሲሆን ለውጥን ተከትሎ ወቅታዊ ማድረግ የሚያስፈልግ ሆኖ ሁሉም የካዳስተር ዓይነት መሰረት የሚያደርገው በህጋዊ ካዳስተር የተዘጋጀውን የካዳስተር ካርታ ነው:: ሌሎች መረጃዎች ተደማሪ እየተደረጉ ወደ ሁለገብ ካዳስተር ሥርዓት የሚያድግ ይሆናል፡፡

የህጋዊ ካዳስተር ዝርጋታ ተግባራዊ መሆን የሚያስገኛቸው ፋይዳዎችን በተመለከተ፦

***

👉በአገር ደረጃ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋለውን የተወሳሰበ ችግር ይህ የአሰራር ስርአት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት ይሄን ችግር በመሰረታዊነት እንደሚፈታ ይታመናል፤

👉በዘርፉ የግብይት ስርአቱን ቀላል፣ ግልፅ፣ ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባሻገር በአገር ኢኮኖሚ እድገቱ ላይ የራሱን አውንታዊ ሚና መጫወት ይችላል፤

👉በዘርፉ በመረጃ አያያዝ ጉድለት የነበረውን ችግር ተጠቅመው ጥቂቶች አላግባብ የሚበለፅጉበትንና ህጋዊ ባለይዞታዎችን ለተለያዩ ጉዳቶች ይዳርግ የነበረውን የአሰራር ችግር ሊፈታ ይችላል ተብሎ ይታመናል፣

👉በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ በዘመናዊ መንገድ የሚደራጀው የከተማ መሬት ይዞታ መረጃ አዳዲስ ፖሊሲዎችን፣ አሰራሮችንና ህጎችን ለማመንጨት የተሻለ ግብአት ሆኖ ያገለግላል፤

👉የከተማ አስተዳደሮች የሚያስተዳድሩትን መሬት ቆጥረው እንዲያውቁ፣ የትኛውን መሬት ለየትኛው አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸው አቅደው እንዲሰሩና በተገቢው መንገድ እንዲያስተዳድሩ ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸዋል፤

👉ከተሞች ከመሬት ሃብታቸው መሰብሰብ የሚገባቸውን ግብር እና ኪራይ በተገቢው መንገድ በመሰብሰብ ለከተማው የመሰረተ-ልማት ግንባታ በማዋል ከተሞች በስርአቱ ያድጋሉ፣ የከተማው ነዋሪም የልማቱ ተጠቃሚ እንዳሆኑ ማድረግ ያስችላል፤

👉የካዳስተር ስርአቱ በሚፈጥረው የመረጃ ምልዑነት በከተማ መሬት ይዞታ የሚስተዋለውን በዜጎች መካከል የሚፈጠረውን ክርክር ይቀንሳል፣ በዚህ ምክንያት የሚያጠፋውን ገንዝብ፣ ጊዜ እና የፍትህ መጓደል ይቀንሳል፤

👉ማንኛውም ዜጋ በከተማ መሬት ይዞታ ዘርፍ ማግኘት የሚፈልገውን መረጃ ብዙ ውጣውረድ ሳይገጥመው በቀላሉ እንዲያገኝ ያደርጋል፤

👉በከተሞች ህጋዊ ካዳስተርን መገንባት ከተቻለ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች እምነት ስለሚያሳድሩ ሃብታቸውን ልማት ላይ ያውላሉ በዚህም ነዋሪው ተጠቃሚ ይሆናል፣ ከተሞች ያድጋሉ፣ ሳቢም ይሆናሉ፤

👉በዘርፉ ሙያ ለተሰማራው አመራርም ሆነ ባለሙያ የእውቀት ሽግግር እንዲፈጠር ያደርጋል፣ አቅምም ይገነባል፣ በዚህም በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

RELATED ARTICLES

Most Popular

Recent Comments